image
tmceth ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ በቤተ ክርስቲያን ደን ልማት ላደረጉት አስተዋጽኦ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሽልማት ተበረከተላቸው።

ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ በቤተ ክርስቲያን ደን ልማት ላደረጉት አስተዋጽኦ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሽልማት ተበረከተላቸው።
ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም [ተ.ሚ.ማ/ አዲስ አበባ]
ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ የአመልድ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር በደን ልማት ላደረጉት አስተዋጽኦ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሽልማት ተበረከተላቸው።
ሰኔ 4/2017 ዓ/ም በድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት በተከናወነው የዕውቅናው መርሐ ግብር ላይ የምስጋና ወረቀትም ዶክተሩ የሚመሩት አመልድ ኢትዮጵያ ለአበረከተው አስተጽኦ ከቤተ-ክርስቲያን ደን ፕሮጀክት ተጠቃሚዎች ተበርክቶለታል።
ሽልማቱ የሰጡት በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በደራ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኙ የስድስት አብያተ ክርስቲያናት እና የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ተወካዮች ናቸው።
የአብያተ ክርስቲያናቱ ተወካዮች እንደገለጹት በዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ የሚመራው አመልድ ኢትዮጵያ በአካባቢያችን ለሚገኙ ጥንታዊ ገዳማት እና አድባራት ተፈጥሮአዊ ደኖቻቸው እና ይዞታቸወ እንዲጠበቅ፣ ኅብረተሰቡን በማስተባበር አጥራቸው እንዲታጠር እና በአካባቢው ለሚገኙ ድሃ ማኅበረሰቦች የኑሮ ማሻሻያ ድጎማ በማድረግ ያደረገውን ተግባራት አውስተው ተወካዮቹ ምሥጋና አቀርበዋል፡፡
የአመልድ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዓለማየሁ ዋሴ (ፒ.ኤች.ዲ) እንደተናገሩት ለመጀመሪያ ጊዜ ከፕሮጀክት ተጠቃሚዎች መካከል ምስጋና ያቀረቡ መሆናቸውን አውስተው፣ በቀጣይ የቤተ-ክርስቲያን ደንን መሠረት ያደረገ የመልክዐ- ምድር መልሶ ማልማት ፕሮጀክት ሥራ በሌሎች ቦታዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና በአካባቢው የተሠራው ሥራ ዉጤታማ መሆኑን አድንቀዋል፡፡
ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በቤተክርስቲያን የደንና ብዝኃ ሕይወት ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማካሄድ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ግንዛቤ መፍጠር የቻሉ ሲሆን እመጓ፣ መርበብት እና ዝጎራ በተባሉት መጽሐፎቻቸውም አንቱታን ያተረፉ መሆናቸው ይነገርላቸዋል።
©የዘገባው ምንጭ አመልድ ኢትዮጵያ ነው።