"ያለንበት ወቅት ከምንም በላይ የእውነተኛ እረኝነት ሐዋርያዊ ሕይወት የሚያሻበት፤ ቤተ ክርስቲያንንም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት የመምራት ጥበብ በእጅጉ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። “ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ
ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም (ተ.ሚ.ማ/አዲስ አበባ)
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የደቡብ አፍሪካና ምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጾመ ሐዋርያትን አስመልክቶ መልእክት አስተላልፈዋል፤ የብፁዕነታቸው መልእክት ከዚህ እንደሚከተለው ይቀርባል።
"ወሰበኩ ከመ ይጹሙ ጾመ ቅድመ እግዚአብሔር፤ በእግዚአብሔር ፊት ጾም ዐወጁ።" ኤር ፴፮፥፱
በቸርነቱ ብዛት ኃጢአታችንን ይቅር ያለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለ፳፻፲፯ ዓ.ም ጾመ ሐዋርያት በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ።
ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን በተቀበሉ ማግስት ወደ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ከመሰማራታቸው አስቀድሞ በጾምና በጸሎት ተወስነው መቆየታቸውን ቅድስት ቤተ ክርስቱያን ታስተምረናለች።
በዚህ በጾመ ሐዋርያት ወቅት የእውነተኛ ሐዋርያዊነት እና አገልጋይነት መሠረቱ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ በማስገዛት ክርስቶሳዊ በሆነ አካሄድ አገልግሎትን ለመጀመር መታመን መሆኑን የምንረዳበት ነው።
ተወዳጆች ሆይ !
ያለንበት ወቅት ከምንም በላይ የእውነተኛ እረኝነት ሐዋርያዊ ሕይወት የሚያሻበት፤ ቤተ ክርስቲያንንም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት የመምራት ጥበብ በእጅጉ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። (ሐዋ ፳፥፳፰)
የሐዋርያት ሕይወት ስለ ክርስትናቸው የተቀበሉትን መከራ ብቻ ሳይሆን ከመንፈሳዊ አገልግሎት የሚገኝ ደስታን ለማግኘት መጓዝ የሚገባንን መንገድ የሚያስተምር ነው፤ ለዚህ ነው በመንፈሳዊ አገልግሎታችን ደስተኞች ሆነን የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል መነሻችን ሊሆን የሚገባው እውነተኛ ክርስቲያንነት እና የክርስትናን ሕግጋት በሕይወት መኖር መሆኑን አበው የሚያስተምሩት።
በምንጾምበት ጊዜም ከጾሙ የምናገኘው በረከት የእግዚአብሔርን በጎ ምላሽ መሆኑን በማመን በልዩ ልዩ መንገዶች ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተጋረጡ የሚመስሉን ችግሮች ከእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት እና ሁሉን ቻይነት የማይሰወሩ አንዳቸውም መከራን እንድንቀበል ከማድረግ በቀር ቤተ ክርስቲያንን አሸንፈው ሊወጡ የማይቻላቸው ነገሮች መሆናቸውን መረዳት ይገባል።
በመጨረሻም :- በዚህ የጾም ወቅት በእግዚአብሔር ፊት በምናቀርበው ጸሎትና ልመና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን በማሰብ በምንሰማራበት ሁሉ አገልግሎታችን ያማረና ለእግዚአብሔር የተመቸ መሆን እንዲችል አብዝተን ልንማጸን ይገባል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
+ አባ ሄኖክ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
