በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት በለገጣፎ ለገዳዲ ኩራ ጅዳ ክ/ከተማ ለገጣፎ ቅሩበ ሳሌም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ከመዘጋት ለመታደግ እንዲያስችል የደብሩ አስተዳዳሪ፣ አገልጋይ ካህናትና የአጥቢያው ምዕመናን በኢትዮጵያ እና በመላው ዓለም ለሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ጥሪ አቅርበዋል።
ደብሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ፈተና ያልተለየውና የአጥቢያው ምእመናንና አገልጋይ ካህናቱም ፈተና የበዛባቸው በፈተናና በመከራ እየተፈተኑ ሃይማኖታቸውን ጠብቀው የሚኖሩ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡
ዙሪያ ገባው በገደል ተከብቦ መውጫ መግቢያቸው የሆነው በር ፈቃዳቸውን በቸሯቸው ትሁን የሌላ ቤተ እምነት ተከታዮች ዛሬ እነርሱ ተነስተው ቦታው ለሌላ ባለሃብት ሊሰጥ በመሆኑ እንደ ቀድሞ እንደልብ መውጣት መግባት፣ መመላለስ አስቸጋሪ ሊሆን መከራውና ፈተናው ከፊት የተደቀነ ሲሆን፤ ስለቦታው እና ስለገጠማቸው ፈተና የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀ ኅሩያን ዮሐንስ መዝገቡ ስለገጠማቸው ፈተና ሲያስረዱ "በአሁኑ ሰዓት ኹለት ነገሮች ገጥመውት ይገኛሉ፤ አንደኛው በጎ ነገር ነው ኹለተኛው ደግሞ የገንዘብ ፈተና ነው። ደብሩ የተሰጠው ቦታ ጠባብ በመሆኑና ከበሩ ባሻገር ያለው ቦታ የእንስሳትና የላሞች ማርቢያ ነው፤ በአገልግሎት ጊዜ አዛባውና እበቱ በሚዛቅበት ጊዜ ሽታው አገልግሎቱን ፈተና ውስጥ ከትቶት ነበር፤ በዚህም ቦታው ወደቤተክርስቲያኗ እንዲካተት ሰበካ ጉባኤውና ምዕመናኑ የጠየቅን ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ለግለሰብ በሊዝ ሊሰጥ መሆኑን ሰምተን መንግሥትን ስንጠይቅ ጥያቄያችንን መንግሥት ተቀብሎ ለቤተክርስቲያኗ እንዲካተት ከፈለጋችሁ ቦታውን በሊዝ ሳይሆን የንብረት ግምት የሞራል ካሳ ግምቱ ከ10,000,000.00-15,000,000.00 [ከአሥር ሚልየን ብር እስከ አሥራ አምስት ሚልየን ብር] ከከፈልን ለቤተክርስቲያኗ እንደሚካተት ነግረውናል በማለት ገልጠውልናል።
አክለውም የደብሩ አሥተዳዳሪ በጎ እድል ያልነው መንግሥት ቦታውን ያለሊዝ መስጠቱ ሲሆን ከበድ ያለንና ችግር ገጠመን ያልነው ይህንን ብር መክፈል ካልቻልን ቦታው በሊዝ ለባለሀብት የሚሸጥ መሆኑ ነው ብለዋል።
ቦታው ከዚህ በፊት ብዙ ፈተና ያስተናገደ መሆኑንና በሀገር ውስጥም በዓለም አቀፍም ርብርብ ተደርጎ የመጣበት ፈተና ያለፈ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የተሰጠን የሦስት ወር የመክፈያ ጊዜ ሊጠናቀቅ በመሆኑ ምዕመናን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ በማድረግ ከመዘጋት ታደጉ ብለዋል።
የመጣውን ፈተና ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተባበር እንደሚወጡት በጽኑዕ ያመኑት ምዕመናን ዛሬም ስለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አማላጅነት በምሽት ደጁ መጥተው የተደረገላቸውን ድንቅ ተአምር ይመሰክራሉ፡፡
የነገ የቤተክርስቲያን እና የሀገር ተረካቢ ሕጻናት የስስት ልጆች ሰንበት ተማሪዎች ይህቺ ቅድስት ቤተክርስቲያን ብትዘጋ የሚደርስባቸውን ጫና እና ፈተና በሕይወታቸው ከሚያጡት በርካታ ነገሮች አነጻጽረው በልጅነት አንደበታቸው ጥሪያቸውን ያቀርባሉ።
ከ150 በላይ ሕጻናትና ታዳጊዎችን ያቀፈው ሰንበት ትምህርት ቤት ኅልውናውን የምንታደገው ዛሬ በምንሰጠው ጥቂት ገንዝብ በመሆኑ፤ ይህ የምንሰጠው ገንዘብ ቤተክርስቲያኗን ከመዘጋት የሚያስቆም ብቻ ሳይሆን ነገ የሚረከቧት የዛሬ ሕጻናት ነገ በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ የሚያደርግ ነው በማለት የሕጻናቱ መምህራን ገልጸዋል።
ድጋፍ ለማድረግ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000241845501
