image
tmceth "እዌድሰኪ ኦ ድንግል በከመ ገብርኤል መልአክ ቡርክት አንቲ ወቡሩክ ፍሬ ከርሥኪ፤ ድንግል ሆይ መልአኩ ገብርኤል እንዳመሰገነሽ እኔም ቡርክት ነሽ ክብርት ነሽ የማኅፀንሽም ፍሬ ቡሩክ ነው እያልኩ አመሰግንሻለሁ" አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (መጽሐፈ ሰዓታት)

ተወዳጅ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ! እንኳን ለፀሐይ መውጫ ለሁለተኛይቱ ሰማይ ለብርሃን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደት በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የቀደሙ አባቶች ከነቢያት ጀምሮ በልዩ ልዩ ምሳሌ አመስግነዋታል። በተለያየ መልኩ ትንቢት ተናግረውላታል፣በእርስዋ ውስጥ ስለተፈፀመው አስደናቂ አምላካዊ ሥራ በረቀቀ ሁኔታ አምልተውና አስፍተው አስተምረዋል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጨለማ ውስጥ የተገኘች የብርሃን እናት፣ በውድቀታችን ውስጥ ያገኘናት መነሻችን፣ ቀና ያልንባት መመኪያችን፣ መሸጋገሪያ ድልድያችን ናት። (ኢሳ ፩፥፱)


ይህችን የአምላክ እናት፤ከተከበሩ ሁሉ የተከበረችውን ርኅርኅተ ሕሊና ለማመስገንና ለማክበር እንደ ቅዱስ ገብርኤል የአምላክን ፈቃድ እንደ አባ ጊዮርጊስ መመረጥን እና እንደ ኤልሳቤጥ መባረክን የሚፈልግ ነው። (ሉቃ ፩፥፳፱፣ ሉቃ ፩፥፵፪)


የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን 


ኦርቶዶክሳዊ ነገረ ሃይማኖትን ለመረዳት እና ለመከተል መመረጥ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ኦርቶዶክሳዊ አስተምሕሮ በንጹሕ ልቡና ሊረዱት እና ሊያውቁት በመውደድ የሚያደርጉት እንጂ በዘፈቀደና ያለ ልክ የራስን ትርጉም በመስጠት የሚያደርጉት አይደለም። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያልተበረዘ እና ቀጥተኛ የሆነ አስተምሕሮ ያላት በመሆኑ ከእኛ የሚጠበቀው መስመሩን በጥንቃቄ መከተል ነው። 


ከሰሞኑ በአንዳንድ ንግግሮች የደረሱ ስብራቶችም በኦርቶዶክሳዊ ነገረ ሃይማኖት ላይ በተለያየ መልኩ ሲነሱ የቆዩ ሃሳቦችም በቀደሙ አባቶች ትምህርት መሠረት እና በኦርቶዶክሳዊ መረዳት ሊጠገኑ ይገባል። 


ተወዳጆች ሆይ ! 


የመመኪያችን ዘውድ የንጽሕናችን መሠረት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እነሆ ተወልዳለች፤ ቅዱስ ጳውሎስ ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ እንዲል (ሮሜ ፲፪፥፲፭) በእመቤታችን መወለድ ደስ ካላቸው ኢያቄም ወሐና፣ የቀደሙ አባቶች እና ከምእመናን ጋር በአንድነት ፍፁም ደስታን እየተደሰትን አምላካችንን እናመሠግናለን።


በመጨረሻም:- በዓለ ልደታ ለማርያምን በምናከብርበት ወቅት ትንሣኤያችን ክርስቶስን የወለደች እመ አምላክን በማመስገን በስምዋም የተራቡትን በማብላትና በማጠጣት በትሕትና እና በፍቅር በአንድነት ጭምር ሊሆን ይገባል። 


እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !

ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

አሜን !



+ አባ ሄኖክ 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 


ሚያዝያ ፴ ቀን ፻፳፲፯ ዓ.ም 

አዲስ አበባ፤ኢትዮጵያ