image
tmceth የቅድስት ቤተክርስቲያንን ክብር በጠበቀ መልኩ ከሁሉም ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ሥራ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አመለከቱ።

የቅድስት ቤተክርስቲያንን ክብር በጠበቀ መልኩ ከሁሉም ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ሥራ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አመለከቱ። ዛሬ በመንበረ ፓትርያርክ ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ላለፉት ሦስት ዓመታት በዋና ሥራ አስኪያጅነት እና በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት ላገለገሉ እንዲሁም በተመሳሳይ ኃላፊነት ለመጪው ሦስት ዓመታት ለሚያገለግሉ ብፁዓን አባቶች በተዘጋጀው የአቀባበልና የምስጋና መርሐ ግብር ላይ በቤተክርስቲያን አንድነት፣ ልማትና ሰላም አስፈላጊነት ዙሪያ ልዩ ልዩ መልእክቶች ተላልፈዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት የቅድስት ቤተክርስቲያንን ክብር በጠበቀ መልኩ ከሁሉም ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ሥራ በጋራ መሥራት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው የቀደሙትን ባለውለታዎች ሳንረሳና ለሠሩትም ሥራ ዕውቅና በመስጠት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማስፈጸም ሀገራችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ ከፍታ የሚያወጣ፣በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ምእመናንና ለሌሎቹም የሚጠቅም ሥራ በመሥራት ለተሻለ ውጤት ልንበቃ ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ያለ ትብብር ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም ያሉት ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤ ራሳችን ዝቅ በማድረግ ከቅዱስ ፓትርያርኩ እና ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጠውን መመሪያ እየተቀበልን በሞቱ የዳነውን በደሙ የከበረውን ሕዝበ ክርስቲያን መጠበቅና በአግባቡ ማገልገል ይኖርብናል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም የመንፈስ ቅዱስ ልጅነትን ከማግኘት ጀምሮ ከንዑሳን መዐርጋት እስከ ዐበይት መዐርጋት የደረሱ አባቶችና በውስጥም በውጭም ያሉ የቤተክርስቲያን ልጆች ራስን ለቤተ ክርስቲያን ቀኖና ማስገዛት፣ ከሐዋርያዊ መንበር የሚወስነውን ውሳኔ እንዲሁም የሚሰጠውን መመሪያ አክብሮ መቀበል፣ ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት እንጂ ባርነት አለመሆኑን ዐውቀው እርስ በእርስ መነቃቀፉን በመተው ለቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት መጽናት አንድ መሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በማጠቃለያ መልእክታቸው፡- “ከእርሰ በእርስ ልዩነቶች የሚጠብቀን የጋራ የሆነ የትኩረት አቅጣጫ እንዲኖረን፣ ነባሩን የቤታችንን መልክ እግዚአብሔር በሰጠን በቤቱ ሕግ ማስቀጠል እንድንችል ለሁሉም ውሉደ ቤተ ክርስቲያን ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡” በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አጠናቀዋል፡፡ .