ከሰሞኑ በተጠናቀቀው 132ኛው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመረጡት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በአቀባበል መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት “የ2017 ዓ.ም የግንቦት ርክበ ካህናት ለቀጣይ ሦስት ዓመታት ቤተ ክርስቲያኒቷን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንድንመራ አባቶች አደራ ሰጥተውናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም አደራው እጅግ ከባድ መሆኑን ጠቅሰው በብቃት መወጣት እንድንችል የሁላችንም ኃላፊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከባድና ጥብቅ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቷን ለማገልገል የምናደርገው ጥረት በመንፈሳዊ መሠረት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው “ከነህምያ ትምህርት በመውሰድ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን እንሠራለን” ሲሉም አመልክተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ አያይዘው እንደተናገሩት፡- ቤተ ክርስቲያን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ በመሆኗ እንደ ከዚህ ቀደሙ በዘልማድ ብቻ ልንጓዝ ስለማይቻል፤በውስጥም በውጭም ያለውን በመቃኘት፣ ዕቅድ በማውጣት መንፈሳዊ፣ አስተዳደራዊና ማኀበራዊ ክፍተቶችን ለይቶ ተጨባጭ የመፍትሔ ዕቅዶችን በማውጣት በጥናት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በቤተ ክርስቲያን ተወስነን ከምንሠራው በበለጠ በውጭ ካሉትም የተለያዩ አካላት እና ከመንግሥትም ጭምር በአስተዋይነትና በጥበብ በመቅረብ ቤተ ክርስቲያኒቷ ተከብራ እንድትሻገር ካላደረግን የትውልድ ቅብብሎሽ ሊያደክምብን ይችላል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያን ከመንፈሳዊ አገልግሎቷ ጎን ለጎን ለመላው ሕዝብ በመራራት ልትደርስ እንደሚገባ ጠቁመው፤ የቤተ ክርስቲያኗን የውስጥ ሰላም በማጠንከር በሀገሪቱ ያሉ ዜጎቿ ወደ ሰላም መንገድ መጥተው መነጋገር እንዲችሉ ድርሻዋ ከፍተኛ መሆኑ ታውቆ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
