ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል

image

ዜና መዋዕል

ዜና መዋዕል ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት `

የቀድሞው አባ ተክለ ማርያም ዐሥራት የአሁኑ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በትግራይ ክፍለ ሀገር በአጋሜ አውራጃ በስቡሕ ወረዳ በ1934 ዓ.ም ከአባታቸው ከአቶ ወልደ ጊዮርጊስ፥ ከእናታቸው ከወ/ሮ ከለላ ተወለዱ፡፡ 


ለትምህርት እንደደረሱም ቀሲስ ወልደ ገሪማ ከሚባሉ ካህን ፊደልና ንባብ ተማሩ። ከዚያም የኤርትራ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ማዕርገ ዲቁና እንደተቀበለ በትግራይ ክፍለ ሀገር ተንቤን በሚባለው አውራጃ ውስጥ ጭኽ በሚባለው ታላቅ ገዳም 1949 ዓ.ም በመግባት ገዳሙን ለ 2 ዓመታት እያገለገለሉ፤ ሰዓታትና ቅዳሴ፣ አምስቱ አእማደ ምሥጢርንና ባሕረ ሀሣብን፣ ከመምህር መንግሥተ አብ ገብረ ማርያም፤ ምዕራፍ ጾመ ድጓን ከመምህር ገ/ሥላሴ መዝገብ ቅዳሴን ከመምህር ተስፋ ማርያም ፈንታ ቅኔን ከመምህር ጌጡ ዕንቁ ባሕርይ ተምረው ካጠናቀቁ በኋላ በ1955 ዓ.ም የዚሁ ገዳም አበምኔት ከሆኑትና እንደወላጅ አባታቸው ሆነው ከሚጠሩባቸው ከመምህር ዐሥራተ ጽዮን ማዕርገ ምንኩስናን ተቀበሉ፡፡ 


በዚሁ ዓመት ከብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የትግራይ ክፍለ ሀገር ሊቀ ጳጳስ ማዕረገ ቅስና ተቀበለዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሦስት ዓመት በሊቀ ረድዕነ፣ አንድ ዓመት የገዳሙ ቄሰ ገበዝ በመሆን፤ እንዲሁም በገዳሙ ልዩ ልዩ ተግባሮች አገልግሎታቸውን አበርክተዋል። ከዚህ በኋላ በ1958 ዓ.ም አክሱም ጽዮን ከሚገኙት ከመምህር ገብረ ጊዮርጊስ ጉባኤ ቤት በመግባት የአራቱን ወንጌላት ትርጓሜ፣ ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ ባሕረ ሀሳብ፥ ከተማሩ በኋላ ወደ ጎንደር ክፍለ ሀገር በመዛወር ከዶክተር አባ አየለ ዓለሙ ጉባኤ ቤት በመግባት 14ቱን የጳውሎስ መልእከታት፤ የሐዋርያትን ሥራ፣ የዮሐንስ ራዕይ፡ ኪዳንንና ትምህርተ ኅቡዓትን ተምረው ካጠናቀቁ በኋላ የሐዲስ መምህር በመሆን ተመርቀዋል። 


ከዚህ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ወደመነኮሱበት ገዳም ተመልሰው ሐዲስን በማስተማር ላይ እንዳሉ በ1964 ዓ.ም መጨረሻ 

ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በመንበረ ፀባዖት ካቴድራል በቅዳሴና በልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎት ተመድበው እየሠሩ ዘመናዊ ትምህርትን በመከታል ላይ ሳሉ በ1968 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ተክለሃይማኖት ሲመረጡ በጊዜያዊ ጉባኤ መራጭነት የፓትርያርኩ አቡነ ቀሲስና ምክትል ልዩ ጸሐፊ በመሆን በማገልገል ላይ እንዳሉ ለኤጲስ ቆጶስነት ለመመረጥ በቅተዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ማዕርገ ቁምስናን ተቀብለዋል። 


የጵጵስና ማዕርግ ካገኙ በኋላ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀጳጳስ በመሆን ተሹመው በተጣለባቸው ኃላፊነት ሐዋርያዊውን አገልግሎት በመስጠት ላይ እንዳሉ ከሦስት ዓመት የኢየሩሳሌም ቆይታ በኋላ 1984 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ሀገር ተሻግረው መንፈሳዊ አገልግሎት ሲያበረክቱ ቆይተዋ።


እንዲሁም በ1999 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ወደ መጀመሪያው መንበረ ጵጵስናቸው ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ተመልሰው በአሁኑ ጊዜ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል።


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ እንግሊዝኛ፣ ዕብራይስጥኛ፣ ግሪክኛ እና ዐረብኛ ቋንቋዎችን በሚገባ የሚችሉ  ሲሆን ከሀይማኖታዊ ዕውቀታቸው በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ አለም አቀፋዊ ተሞክሮ ያላቸው ናቸው። 


የ5ተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ዕረፍትን ተከትሎ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም በተደረገ የፓትርያርክ ምርጫ ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በመሆን በመንበረ ተክለሃይማኖት ላይ 63ተኛው እጨጌ እና 6ተኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ በመሆን ተሹመዋል።