ብሉይ ኪዳን
ብሉይ ኪዳን
ኪዳን - ኪዳን ማለት በሁለት ወገኖች መካከል የሚደረግ ውል (ስምምነት) ማለት ነው:: እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር ያደረገው ውል፣ ስምምነት ማለታችን ነው::
በዚህ መሰረት ለኪዳን ሁለት ወገኖች ያስፈልጋሉ:: ውል ሰጪና ውል ተቀባይ፤ ከዚያም መኃላው (ኪዳኑ) ይኖራል:: እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ከፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በኪዳኑ አልተለየውም:: (ዘፍ 1፤26-28)
ብሉይ - ማለት የቆየ፣የጥንት፣የበፊት፣ቀዳማዊና የድሮ ማለት ነው:: ብሉይ ኪዳን ማለት ጥንታዊ፣ቀዳማዊ ውል (ስምምነት) ማለት ነው:: ይህ ውል በሙሴ አማካኝነት እግዚአብሔር ለእስራኤላዊያን የገባውን ኪዳን የያዘ ነው::
ይህ ኪዳን ከፍጥረት ዓለም እስከ ክርስቶስ መወለድ ድረስ ያለውን ታሪክ በውስጡ የያዘ ነው:: የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት ከ1400-400 ዓ.ዓ(ቅ.ል.ክ) ድረስ ባሉት 1000 ዓመታት ውስጥ ነው:: የተጻፈውም ሰላሳ ሁለት (32) በሚደርሱ አባቶች ነው። የተጻፈውም በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው።
ብሉይ ኪዳንን ብሉይ ኪዳን ያሰኘው እግዚአብሔር አምላካችን ከእስራኤል ዘነፍስ ጋር ያደረገው አዲስ ውል ወይም ስምምነት (ሐዲስ ኪዳን) ሲመጣ ነው።
(ኤር 31፤31 ማቴ 26፤26-29 1ኛ ቆሮንቶስ 11፤25-26)
ብሉይ ኪዳን ተሽሯል የሚለው አስተምህሮ የተሳሳተ ነው።
ብሉይ ኪዳን በሐዲስ ኪዳን መምጣት ጸንታለች፣ ከብራለች::(ማቴ 5፤19-20) ጌታችን ወንጌልን ሲያስተምር ከብሉይ ኪዳን እየጠቀሰ ማስተማር ለዚህ በቂ ማሳያ ነው። ‹‹ሕግና ነቢያትን ልሽር የመጣሁ አይምሰላችሁ ልፈጽም እንጂ›› ማቴ 5፤17። በሕግና በነቢያት ስለ እርሱ የተነገሩትን ለመፈጸም የወጣ መሆኑን አስተምሮናል:: ስለዚህ ብሉይ ኪዳን የሐዲስ ኪዳን ምስክር ፣ንባብ፣ትርጓሜ፣ፍጻሜ ናት:: ቅዱስ አውግስጢኖስ የተባለው የቤተ-ክርስቲያን ሊቅ ‹‹ሐዲስ ኪዳን በብሉይ ኪዳን ተሰውሯል፡፡ ብሉይ ኪዳን በሐዲስ ኪዳን ተገልጧል›› በማለት ተናግረዋል::
የሁለቱ ኪዳናት አንድነት
ሁለቱም ኪዳናት የሚገለጡት (የሚስተማሩት) ስለ እግዚአብሔር ነው:: በብሉይ ኪዳን የተገለጠ እግዚአብሔር በሐዲስ ኪዳን የተገለጠው እሱ እራሱ ነው:: ሁለቱም ስለተመረጡ ሕዝቦች ይናገራሉ:: በብሉይ ኪዳን የተመረጡ ሕዝቦች የሚባሉት እስራኤላዊያን (ዘስጋ) ሲሆኑ በሐዲስ ኪዳን የተመረጡ ሕዝቦች ክርስቲያኖች (እስራኤል ዘነፍስ) ናቸው:: ሁለቱም በቅዱሳን ሰዎች በእግዚአብሔር መሪነት የተጻፉ ናቸው::
የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ክፍሎች
የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተህምሮ መሠረት ብዛታቸው አርባ ስድስት (46) ሲሆን በ4 ዋና ዋና ክፍሎች በመከፈል ይጠናሉ።
እነርሱም፡-
ሀ. የሕግ ክፍል (ብሔረ ኦሪት) /Tora/
በሙሴ አማካኝነት የተጻፉ 5 የሕግ መጽሐፍቶች በውስጡ ይዟል::
እነርሱም ኦሪት ዘፍጥረት፣ኦሪት ዘጸአት፣ኦሪት ዘሌዋውያን፣ኦሪትዘኁልቊ እና ኦሪት ዘዳግም፣ ናቸው::
ለ. የታሪክ ክፍል (ከቱቢም-kethubim)
የታሪክ መጻሕፍት ክፍል በውስጡ 17 መጽሐፍቶችን ይዟል:: እነርሱም-
1.መጽሐፈ ኢያሱ
2.መጽሐፈ መሳፍንት
3.መጽሐፈ ሩት
4.1ኛ እና 2ኛ ነገስት
5.መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊና ካልዕ
6.1ኛ ዜና መዋዕል
7.2ኛ ዜና መዋዕልና ጸሎተ ምናሴ
8.መጽሐፈ ዕዝራነህምያ
9.መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል እና መጽሐፈ ዕዝራ ካልዕ
10. መጽሐፈ ጦቢት
11.መጽሐፈ ዮዲት
12.መጽሐፈ አስቴር
13.መጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ
14.2ኛና 3ኛ መቃብያን
15.መጽሐፈ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን
16.መጽሐፈ ኩፋሌ
17.መጽሐፈ ሄኖክ
ሐ. የመዝሙርና የጥበብ መጻሕፍት
1. መጽሐፈ ኢዮብ
2. መዝሙረ ዳዊት
3. መጽሐፈ ተግሳጽ
4. መጽሐፈ መክብብ
5. መኃልየ መኃልየ ዘሰሎሞን
6. መጽሐፈ ጥበብ
7. መጽሐፈ ምሳሌ
8. መጽሐፈ ሲራክ
መ.የትንቢት መጻሕፍት
የትንቢት መጻሕፍት በውስጡ 16 መጻሕፍትን ይዟል፡፡ከአስራ ስድስቱ መካከል አራቱ ዐበይት ነቢያት ሲሆኑ 12ቱ ደግሞ ደቂቀ ነቢያት ተብለው ይጠራሉ፡፡
1.ትንቢተ ኢሳይያስ 9.ትንቢተ አብድዩ
2.ትንቢተ ኤርሚያስ 10.ትንቢተ ዮናስ
3.ትንቢተ ሕዝቅኤል 11.ትንቢተ ናሆም
4.ትንቢተ ዳንኤል 12.ትንቢተ ዕንባቆም
5.ትንቢተ ሆሴዕ 13.ትንቢተ ሶፎንያስ
6.ትንቢተ አሞጽ 14.ትንቢተ ሀጌ
7.ትንቢተ ሚክያስ 15.ትንቢተ ዘካርያስ
8.ትንቢተ ኢዩኤል 16.ትንቢተ ሚልክያስ
Old Testament `
